Geschichte

Jul 1, 2012 by     1 Comment     Posted under: Gemeinde

ይህ ታሪክ በሐምሌ ወር ፳፻ ዓ. ም. የአጥቢያችንን ፲፭ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ ሰናከብር በታተመው መጽሔት ላይ ዲ/ መታፈሪያ የጻፈውና ያወጣነው ነው።

የኑርንበርግ ቅ/ሥላሴ ቤተክርስቲያን ታሪክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

መጀመሪያ የሌለው ያልነበረበት ጊዜ የሌለ መጨረሻም የሌለው የማይኖርበት ጊዜ የማይኖር የሁሉ ነገር ፈጣሪ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ከዚያም „በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን ፈጠረ“ ዘፍ፣1.1 ከሚለው ሃረግ ጀምሮ የተፈጠሩ ፍጥረቶች የተሰሩ ስራዎች የተከሰቱ ክስተቶች ሁሉ በዚህ ጊዜ የሚባል መነሻ አላቸው። በተለይም ስለአንድ ታሪክ ሲወሳ መቼ ተጀመረ? በማን ተጀመረ? እንዴት ተጀመረ? ያለቀ ታሪክ ከሆነ እስካለቀበት በሂደት ላይ ያለም ከሆነ እስካለበት እንዴት ተካሄደ? የሚሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች በተቻለ መጠን መመለስ አለበት። አሊያ ታሪኩ ታሪክ ሊሆን ሊባልም አይችልም። ከዚህ ሌላ አንድ ታሪክ ከጅምሩ ጀምሮ እስከደረሰበት ደረጃ ድረስ በሂደቱ ውስጥ መጥፎም በጎም አጋጣሚዎች ይኖሩታል ታሪክ ሰሚው ወይም አንባቢው ከሁለቱም በመማር የራሱን ሂደት ሊመረምርና ሊያስተካክልበት ይችላል።

ስለዚህ በጆሮየ የሰማሁትን በአይኔ ያየሁትን እና በውስጡ ያለፍኩበትን፣ በአእምሮየ የማስታውሰውንና በማስታወሻዬ የመዘገብኩትን እንደነበረው ለማስቀመጥ፡ ምናልባት ራሱን የቻለ መጽሐፍ ሊሆን ስለሚችል ለዚህ የበዓል ዝግጅት የሚስማማውን ዋናዋናውን ለማስቀመጥ እሞክራለሁ። እዚህ ላይ ታሪኩ እንደማንኛውም ታሪክ አስደሳችም አሳዛኝም አኩሪም አሳፋሪም ሂደቶች ሊኖሩት ይችላል ስለዚህም አንባቢዎቹን በተለይም ደግሞ የዚህ ታሪክ ገጸባህሪያት ብዙ እንደመሆናቸው ሁሉን ላያስደስት ይችላል የሚል ግምት አለኝ። እዚህ ላይ ለማሳሰብ የምወደው ነገር ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው ማንኛውንም ግለሰብ ለማስደሰት ወይም ለማሳዘን ታስቦ አለመሆኑን ነው። የዚህ ጽሑፍ ዋና አላማ፣

1. የቤተክርስቲያኒቱ ታሪክ ሳይዛባ በሁሉም ገጽታዎቹ እንዳለ ለትውልድ እንዲቀመጥ

2. በተመሳሳይ ጉዞ ላይ ለሚገኙ ሁሉ ትምህርት ሊሰጥ ስለሚችል

3. በዚህ ታሪክ ውስጥ በተለያየ አቋምና አመለካከት የተጓዙት ሁሉ ዛሬ ከደረሱበት ደረጃ ላይ ሆነው ያለፈውን በመቃኘት ራስን መርምሮ ድክመቶችና ስህተቶች ታርመው ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው በአንድ ሃሳብ ወደፊት ለመጓዝ እንዲቻል፡ ራሳችንን የምናይበት መስታወት እንዲሆን ነው።

በሃገራችን በነበረው የመንግስት ለውጥ ምክንያት ከ፲፱፻፹፫ (1991)እስከ ፲፱፻፺፪ (1996) ዓ.ም ማብቂያ
ድረስ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከተለያየ አገር በተለይ ወጣቱ በብዛት በስደት ወደጀርመን የጎረፈባቸው አመታት ነበሩ። ከ፲፱፻፹፫ (1991) ዓ.ም ጀምሮ በሃገራችን መንፈሳዊ ስሜት የተጋጋለበት፣ ወጣቱ በቤ/ክርስቲያኑ ዙሪያ የተሰባሰበባቸው፣ ስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ሰ/ት/ቤቶች በየቦታው መደራጀትና መጠናከር የጀመሩባቸው አመታት ነበሩ። በእነዚህ አመታት ከሃገሩ በተለያዩ ምክንያቶች የተሰደደው ወጣት፡ ይህንን መንፈስ ስንቅ እድርጎ ሲሆን፡ በውጪ የቆየው ደግሞ የሐገሩ የወገኑ ናፈቆት የሚያንገበግበው ነው። የነዚህ ሁሉ መገናኛ በተለይ በጀርመን አገር የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ነው። በዚህ ጣቢያ ውስጥ ብዙ አስደሳች ነገሮች ይታያሉ፡ ለምሳሌ አዳዲስ ስደተኞች ሲመጡ ተቀብሎ ማስተናገድ፣ እርስ በእርስ መጽናናት፣ ከመንግስት ለሚቀርበው ጥያቄ አንዱ ሌላውን ማዘጋጀት፣ ወገናዊ ፍቅር፣ የልብ ጓደኝነት፣ ከዚያም አልፎ ለትዳር መተሳሰብና ለቁምነገር መብቃት ጥቂቶቹ ናቸው።

ከሃገራቸው የመሰባሰብን፣ የእግዚአብሔርን ቃል የመስማትን፣ በካህን የመባረክንና የመጽናናትን ልምድ አዳብረው የመጡት ተሰባስበው፡ ከመካከላቸው በመንፈሳዊ እውቀቱ ሻል ያለውን እንዲያስተምራቸው ማበረታታት፣ መስቀል ለመሳለም ይፍቱኝ ለማለት ቤ/ክን ያለችበትን ካህን ያለበትን ማጠያየቅ የተለመደ ነው። በዚህ መሻት ውስጥ በተለያዩ ነገሮች በመደለልና በማስመሰል የድርሻውን ለማግኘት የመናፍቃኑ ሩጫና ወከባ መጠነ ሰፊ ነበር። በዚህም ምክንያት ጥቂት የማይባሉ ወገኖች ሰለባ ሆነው ቀርተዋል። ትንሽ ጠንከር ያሉት ኦርቶዶክሳዊያን ደግሞ በቅናት በመነሳሳት የበለጠ ለመጠንከር የሚያስችላቸውን መንገድ ከማፈላለግ አልቦዘኑም። የዛሬዋ የኑርንበርግ ቅ/ሥላሴ ቤ/ክን መሠረት ለመጣልና እዚህ ደረጃ ለመድረስ ምክንያት የሆነው ከእንደነዚህ አይነት ወጣቶች መካከል የዚህ ታሪክ ጀማሪ ለመሆን እድል የገጠማት እህት፡ ከስሜቷ ማህጸን ውስጥ በፈለቀ የቅናት ትኩሳት እንደተነሣሣች ትተርካለች።እንዲህ ነበር

እስከ ፲፱፻፹፭ (1993) ዓ.ም ድረስ በኑርንበርግ ከተማ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ብዙ ባይባሉም ጥቂት ግን አልነበሩም። ሆኖም የቤተክርስቲያን ድምፅ የመስማት የካህን መስቀል የመሳለም እድል አልነበራቸውም፡ ምንም እንኳን ቤ/ክን በጀርመን አገር በከለኝ የነበረች ቢሆንም የኑርንበርግ ነዋሪዎች አልተዋወቋትም። በ፲፱፻፹፬ (1992)ዓ.ም ቤ/ክን ከሰሜን ጀርመን ወደደቡብ ዘልቃ በሙኒክና በእሽቱትጋርት ልጆቿን እያፈላለገች እየሰበሰበች ነው፡ ኑርንበርግ ግን አልደረሰችም እነዚህን ምስኪኖች መናፍቃን ያዋክቧቸዋል እያለው እንደሌለው ሆነው በቅናት በቁጭት ይቃጠላሉ፡ ከዘመድ ጋርም ሲደዋወሉ ወይይቱ ስለብቸኝነት ስለመንፈሳዊ ነገርና ስለእግዚአብሔር ቃል ረሃብ ነው፡ ታዲያ አንድ ቀን እንዲህ ሆነ። ከእነዚህ መካከል እንዲት እህት (ወሪ/ት አብነት ታዬ) ዘመድ ለመጠየቅ ወደ ካርልስሩሄ ስልክ ትደውላለች ከዚያም እሽቱትጋርት ቤክ/ን ስላለ እዚያ ውለው ደስ ብሏቸው እንደተመለሱ ይነግሯታል፡ እንዲያውም የካህኑ መኖሪያ ለኑርንበርግ ቅርብ በሆነው በሙኒክ ከተማ መሆኑንና በቅርበትም እንደሚተዋወቁ ጭምር ስትረዳ፡ የካህኑን ስልክ ተቀብላ ለመደወል እጮኛዋን (ዳንኤልን) እንኳን ለማማከር እቤት እስኪገባ ድረስ ለመጠበቅ ጊዜ እንዳልጨረሰች ወ/ሮ አብነት ትገልጻለች፡ (ፎቶ) ወዲያውኑ ወደሙኒክ ትደውልና ችግሩንና ፍላጎቷን በአጭሩ ለቀሲስ መስፍን ታስረዳለች። እሳቸውም በደስታ ሐሳቧን ተቀብለው እንዲያውም የሚያገናኛቸው በማጣት እንጂ ለመምጣት ሃሳቡ እንዳላቸው ገልጸውላት፡ ቀጠሮ ይዘው ይለያያሉ። ያን ጊዜ የነበረው የስደተኞች መጠለያ ሽሎስ የሚባለው ስለነበረ እሷም የምትኖረው እዚያው በመሆኑ ለነበሩት ወገኖች በሙሉ የምስራቹን ትነግራለች ቀጠሮውንም ታሳውቃለች በግል ለሚኖሩትም ሁሉ ዜናው ይሰራጫል የቀጠሮው ቀን በጉጉት እየተጠበቀ ደረሰ።

ሰኔ ፱ ቀን ፲፱፻፹፭ (16.06.1993) ዓ.ም ኦርቶዶክሳዊ ካህን ኑርንበርግን እረገጣት። አብነት ከእጮኛዋ ጋር ሆና ባቡር ጣቢያ ተቀበለቻቸው፡ የናፈቀችውን መስቀል ተሳለመች፡ ቤክ/ን ልጆቿን ፍለጋ ሽሎስ መጠለያ ጣቢያ ገባች። ሰፋ ያለው ክፍል ተመርጦ፡ በተቀጠረው ስዓት ሃያ አካባቢ የሚሆኑ የመጀመሪያዎቹ መዕመናን ተሰባሰቡ። (ፎቶ)ቄሱ አስተማሯቸው፣ አጽናኗቸው፣ ለትዝታ ያህል „አብነት“ የሚለውን ስም መነሻ በማድረግ እያንዳንዱ ሰው ልክ እንደ እህታችን ለመልካም ነገር አብነት መሆን እንደሚገባው መከሩ፡ ለመታሰቢያም እንዲሆን በአንድነት ሆነው ፎቶግራፍ ተነሱ። አብዛኛዎቹ የደስታ እንባ ሲተናነቃቸው እንደነበረ በወቅቱ የነበሩት ያስታውሳሉ። ኑርንበርግ ተባረከች፣ እግዚአብሔር ጎበኛት፣ መሠረቱንም ተከለ።

ይህንን የመሰለው በእግዚአብሔር ስም መሰባሰብ እንዲቀጥል ውይይት ተደረጎ ቋሚ ኮሚቴ እስኪመሠረት ድረስ ቦታ ለማፈላለግና አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለማከናወን ወሪ/ት አብነትን እንዲረዳት ከነበሩት መዕመናን ውስጥ አቶ ካሳሁን እሸቴ ተመርጦ ተወከለ። ይህንን ዜና የሰማው ሁሉ ቦታ ማፈላለጉን ተረባረበ፡ ስለዚሀም እስከዛሬ ድረስ የምንሰባሰብበት „ሳንት ኩኒጉንድ“ የካቶሊኮች የጸሎት ቤት ተገኘ።

ሰኔ ፳፮ ፲፱፻፹፭ (03.07.1993) ዓ.ም ካህኑ በተገኙበት የመጀመሪያው አራት (4) አባላት ያሉት ኮሚቴ ተዋቀረ። አነዚህም፣-

1. አቶ ካሳሁን እሸቴ

2. ወ/ሪት አብነ ታዬ

3. አቶ ዳንኤል ብርሃኔ

4. አቶ ደሲሳ ኢራና ነበሩ።

ካህኑም በየሁለት ሳምንቱ ቅዳሜ ለመምጣት ቃል ገብተው በዚሁ መሠረት የኑርንበርግ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ለአንድ አመት ከዘጠኝ ወር ያክል ቀጠለ።

(ከዚህበላይየተገለጸውታሪክበወቅቱከነበሩትየተረዳሁትነው)

የእሁድ አገልግሎት አጀማመር

ሚያዚያ ፰ ቀን ፲፱፻፹፯ (15.04.1995) ዓ.ም ዕለተ ሆሣዕና

በ፲፱፻፹፯ (1995) ዓ.ም ከምንጊዜውም በላይ የስደተኛው ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ስለዚህም የመጠለያ ጣቢያዎች በብዛት ተከፍተዋል ከእነዚህ አንዱ ፎይሽት የሚባለው መጠለያ ጣቢያ ሲሆን፡ ይህ ቦታ እንደ ቋሚ መጠለያም እንደመተላለፊያም(ትራንዚት) ሆኖ ስለሚያገለግል፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ይኖሩበታል። እኔም በዚህ ዓ.ም ከገቡትና በዚህ ቦታ ከተመደቡት አንዱ ነበርኩ። አንድ ቀን ዛሬ ሆሣዕና ስለሆነ፡ እንሰባሰብ እዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምር ልጅ አለ፡ ተባለ፡ በመገረም፣ በመጓጓት፣ በመደሰት፣ ብቻ በተቀላቀለ ስሜት የልጁ(የዘነበ) መኖሪያ ክፍል እስኪጨናነቅ ድረስ ሞላነው። መርሃግብር መሪው ቆሞ እለቱን አስተዋወቀ፣ የሆሣዕና መዝሙሮች ተዘመሩ። ከዚያም መምህሩን አስተዋወቀና ተቀመጠ። መምህሩም ስለሆሣዕና በረጅሙ አስተማረን የመዝሙር ችሎታም ስላለው በግሉ ዘመረልን። አንዳንዶቻችን ከሃገራችን ከወጣን
ረዘም ያለ ጊዜ ስለሆነን እንደዚህ አይነት ጉባኤ አይተን አናውቅም፡ ናፍቆትም ተጨምሮ ነው መሰለኝ ስሜታችን ተነካ። መርሃ ግብሩ እንዳለቀ እርስ በእርስ ተዋወቅን። መሪው ዮናስ ብዙነህ አስተማሪው የአሁኑ ዲያቆን የወቅቱ ዘነበ ወርቁ ነበሩ፡ ከነዚህም ሌላ መንፈሳዊ እውቀትና ልምድ ያላት አንዲት እህት ነበረች፡ (ወሪ/ት ትእግስት ካሳ) ይቺ እህት ለኑርንበርግ ሰ/ት/ቤት ስብከተ ወንጌልና መዝሙር መጠናከር ጉልህ አስተወጽኦ አበርክታለች። በሳምንቱ ትንሣኤን ለማክበር ተሰብስበን ወደሙኒክ ሄድን። የነበረው የበዓሉ ስነስርዓት አገራችን የገባን ያክል አስደስቶን ተመለስን።

የአባታችን የቀ/መስፍን መልካም ፈቃድ ተጠይቆ በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ለቅዳሜ የፈቀዱት የካቶሊክ ቤ/ክን ኃላፊዎች፡ በየሳምንቱ እሁድ እንድንገለገልበት ፈቅደው፡ በብዙ ፈታናዎችና ውጣ ውረዶች እየተንገላታ በእግዚብሔር ቸርነት ሳይቋረጥ እዚህ ደረጃ የደረሰውና ዛሬ ሁላችንም የምናየው ጉባኤ እነሆ በትንሣኤ ሳምንት „ለዳግሚያ ትንሣኤ“ በ13 ሰዎች ተጀመረ። ከዚያ ጀምሮ
በወር ሁለት ጊዜ የነበረው የካህኑ ቀጠሮ በወር አንድ ጊዜ ሆነ።

የሰ/ት/ቤቱ ስያሜ

መስከረም ፳፯ ቀን፲፱፻፹፱ (08.10.1996)
ዓ.ም እስከዚህ ድረስ ሰ/ት/ቤ/ቱ ስያሜ አልነበረውም። በዚህ ቀን ሦስት አማራጮች ጊዮርጊስ አማኑኤል ሥላሴ ተጠቁመው ድምፅ ሲሰጥ የስላሴ በለጠ። ካህኑም አስመርጠው እንደጨረሱ፡ አንድ የሚያስደንቅ ነገር ተናገሩ „አንድ ሰው ህልም አይቶ ነግሮኝ ይህ እንደሚሆን እና እንደማይሆን እየጠበቅሁት ነበር፡ አሁን እንደህልሙ ሆኖ ሳየው በጣም ገረመኝ፡ በሥላሴ ስም መሰየሙን ባለቤቱ ፈቅዶታል“ አሉን። ከዚያን ቀን ጀምሮ „የኑርንበርግ ቅ/ሥላሴ ሰ/ት/ቤ/ት“ በመባል ይጠራ ጀመር።

በሰ/ት/ቤቱ ዙሪያ የሚከናወኑ አገልግሎቶች፣-

1. በየሳምንቱ በተፈቀደልን ቤተጸሎት መዕመናንን በር ከፍቶ ቤት ጠርጎ ወንበር ደርድሮ አስፈላጊ    የሆኑትን ንዋያተ
ቅድሳት አመቻችቶ መቀበልና ስርዓቱ ሲያልቅ እንግዶችን ሸኝቶ እቃ መልሶ ቤት አጽድቶ በር መዝጋት፣

2. በየሳምንቱ በቋሚነት የመክፈቻ ጸሎት፣ መዝሙር፣ ስብከተ ወንጌልና መዝጊያ ጸሎት መርሃግብሮች ይካሄዳሉ። ለዚህም መርሃግብር መሪው ሰባኬ ወንጌሉና ዘማሪያኑ በመናበብ ወጥ የሆነ አገልግሎት ይሰጣል፣

3. አልፎ አልፎ ዶግማና ቀኖና (አዕማደ ምስጢራትና መስጢራተ ቤ/ክን) በተከታታይ ይሰጣሉ፣

4. የሙዳይ ምፅዋት፣ አስራት በኩራት፣ መባዕና ስዕለት ይሰበሰባል፣

5. በየሳምንቱ የሻይና ዳቦ መስተንግዶ ይደረጋል፣

6. በዓላት ይዘጋጃሉ መስተንግዶና ልዩ መንፈሳዊ ዝግጅት ይደረጋል፣

7. የፅዋ ማህበር አገልግሎት በየወሩ ይከናወናል፣

8. መንፈሳዊ የተሳላሚ ጉዞ በህብረት ይደረጋል። እነዚህ በሰ/ት/ቤ/ቱ አባላት ብቻ የሚከናወኑ ሲሆን፣

9. ካህኑ በሚመጡ ጊዜ እንደአስፈላጊነቱ ስርዓተ ቅዳሴ ስርዓተ ጥምቀትና ስርዓተ ጋብቻ ይፈጸማሉ።

የሰ/ት/ቤ/ አሰተዳደራዊ መዋቅር

እንደሚታወቀው በቤክ/ን ስርዓት መሠረት ቤክ/ንን የሚመራት ከካህናትና ከመዕመናን ተውጣጥቶ የተዋቀረ የሰበካ ጉባኤ በመባል የሚታወቀው አካል ሲሆን፡ እዚህ ግን የቤ/ክንን መስፈርት ገና ስላላሟላ ማለትም ታቦተ ህግና የራሱ ካህን ስለሌለው ቤ/ክን ሊባል ስለማይችል፡ አስተዳደሩም በደቡብ ጀርመን ባለው ሰበካ ጉባኤ ስር የተዋቀረ ኮሚቴ የሚባለው አካል ነው።

የኮሚቴው አወቃቀር ከመጀመሪያው እንዳየነው አራት አባላት የነበሩት ሲሆን፡ በíላ የወንጌል አስተማሪው ዘነበ ተቀላቅሎ አምስት አባላት ሆነዋል። የኮሚቴው አመራረጥ፣- በአስር አመት
ውስጥ አገር በመቀየርና በስራ ምክንያት ሲጎድሉ በጊዜው የሚተካ ሲሆን፡ የመጀመሪያውን ሳይጨምር ሁለት ጊዜ የኮሚቴ ምርጫ ተካሂዷል።አመራረጡም ካህኑ የሚወክላቸውን አንድ ሰው ሲመርጡ፡ መዕመናን ደግሞ አራት ሰው ይመርጣሉ። የካህኑ ተወካይ የኮሚቴው ሰብሳቢ በመሆን ከመጀመሪያ ጀምሮ ሰበካ ጉባኤ እስከሚመረጥ እስከ ፲፱፻፺፭ (2003) ድረስ ሰርቷል።

የኮሚቴው የሥራ ድርሻ፣-በኮሚቴ ደረጃ ሲታይ በደንብ የተጠናከረና በሁለገብነት አስተዳደሩን የሚመራ ባይሆንም፡ የማይናቅ አገልግሎት ነበረው፡ ይኸውም በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ ለበዓሉ ዝግጅት አስፈላጊ የሆኑትን ስራዎች በቅንነት ይሠራል። ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ጸሐፊና ገዘብ ያዥ ቢኖሩትም፡ ሁሉም የሥራ ድርሻውን ብቻ በጥንቃቄ የሚሠራ ሳይሆን በቅንነት እንዳደረሰ ብቻ ነበር ያገለግል የነበረው።

ስለዚህ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ካሳሁን እሸቴ በቋሚነት የሙዳየ ምጽዋትና የአስራት ክፍያዎችን ካርኒ በመቁረጥ ይሰበስባል፡ አልፎ አልፎ ሰብሳቢው በሌለበት የተገኘው አባል ይሰበስባል። ይህ ገንዘብ በጊዜው ሰ/ት/ቤ/ቱ የራሱ የሆነ የባንክ ሒሳብ ስለሌለው የካህኑ መቀመጫ ወደሆነው ወደሙኒክ ቅ/ገብርኤል ባንክ እየተላለፈ ለአስር አመት ዘልቋል። በተጨማሪም ሰብሳቢው ጥምቀተ ክርስትናና ሥርዓተ ጋብቻ ለመፈጸም የሚፈልጉ መዕመናን ሲኖሩ ለካህኑ ነግሮ ቀጠሮ በማሲያዝ ነገሮችን ያመቻቻል።

የሰ/ት/ቤቱ መዝሙር ክፍል፣- የሰ/ት/ቤቱ መዘምራን በትምህርት ክፍልና በመዝሙር ክፍል የተዋቀረ ሲሆን፡ የትምህርት ክፍል ሃላፊው ዘነበ የመዘምራኑ ሰብሳቢና በኮሚቴው ውስጥ መዘምራንን ወክሎ አባል እንዲሆን ተደረገ። ከላይ እንደተገለጸው በከሚቴው እምብዛም የተጠናከረ እንቅስቃሴ ስለሌለ በአብዛኛው አስተዳደራዊውና የአገልግሎቱ እንቅስቃሴ የሚከናወነው በመዘምራኑ በኩል ነነበር።

የእሁድ አገልግሎት ሲጀመር የመጀመሪያዎቹ የመዝሙር ክፍል አባላት፣-1.ዮናስ ብዙነህ 2. ዘነበ ወርቁ 3. ዳንኤል ብርሃኔ 4.ወ/ሪት አብነት ታዬ 5.ወ/ሪት ብዙነሽ አብርሃ 6.ወ/ሪት ትዕግስት ካሣ 7.መታፈርያ ወ/ፃድቅ ነበሩ። የመጀመሪያዎቹም መርሃግብር መሪዎች ደግሞ ዮናስና ዳንኤል ሲሆኑ አሰተማሪው ዘነበ ነበር።

የመዘምራን አገልግሎት

በየጊዜው አዳዲስ አባላት እየተጨመሩ ቁጥራቸው እየበረከተ የመዕመናኑም ቁጥር በዚያውልክ ሲጨምር አገልግሎቱም የበለጠ እየተጠናከረ ሲሄድ በየሳምንቱ አስፈላጊም ሲሆን በመሃል በመገናኘት ስለሰ/ት/ቤቱ እንቅስቃሴ ለመወያየት ስብሰባ ይደረጋል።

የስብሰባው አላማ፣- ስለሚዘመሩ መዝሙሮች፣ ስለሚሰጠው ትምህር(ስብከት) ከወቅቱ ጋር የሚስማማ ከሰሚዎቹ ጋር የሚዋሃድ መሆኑን ሁል ጊዜ ይፈትሻሉ። በቅርብ ሆኖ የአገልግሎቱን ሂደት የሚቆጣጠር አባት ስለሌለ፡ እርስ በእርስ መተያየት መወያየት አስፈላጊ ነበር። በየሳምንቱ ስለሚደረገው ጉባኤ ስዓት አከባበር፣የሻይ መስተንግዶ፣ስለምንገለገልበት ቦታ ጽዳት፣ የበዓላት ዝግጅት፣ ሃሳቡን ከማፍለቅ ጀምሮ ተግባራዊ እስከማድረጉ ድረስ ሃለፊነቱ ይሰማቸዋል። ከዚህም አልፎ ለመቅደሱና ለመዝሙር አገልለግሎት የሚያስፈልጉትን ንዋያተ ቅድሳት በአጠቃላይ የጎደሉ ነገሮችን በሙሉ በማሟላት ሃላፊነቱን የሚረከብ ካህን በቦታው እስከሚመደብበት ጊዜ ድረስ ቆይተዋል። በíላም አገልግሎቱ ሲጠናከር ስብሰባው በወር አንድ ጊዜ እንዲሆን ተወሰነ፡ ያለፉትን አራት የአገልግሎት ሣምንታት በመቃኘት ጉድለቶችን ለመሙላት ጠንካራ ጎኖችን ለማጎልበት ይሞከራል። በምንሰባሰብበት ጊዜ ስብሰባችንን እንዲባርክ መለአኩ ቅዱስ ዑራኤልን እናስባለን፡ በስሙም ጸበል ጸዲቅም ይዘጋጃል። ከአገልግሎት በኋላ ድካምና መሰላቸት እንዳይኖር፣ ሰፋ ያለ ጊዜ ለማግኘት፣ እርስ በእርስም ለመግባባትና ለመቀራብ ሲባል፡ ስብሰባው በብዛት ቅዳሜ ቀን በተራ በየቤታችን ይደረጋል። በዚህ ስብሰባ ላይ ስለአገልግሎት ብቻ ሳይሆን ስለግልና ማህበራዊ ህይወታችን፡ አንደኛው ቋሚ የመወያያ ርዕሳችን ነው። ስለዚህም አባላቶቻችን ሥርዓተ ጋብቻ ሲፈጽሙ ልጅ ሲወልዱ ማስታወሻ የሚሆን ተመሳሳይ ስጦታ ይበረከትላቸዋል። ይህ የመሰባሰብ ልማድ በእኔ እይታ በፍቅር መተሳሰርን፣ መደጋገፍን፣ በአገልግሎት መበርታትን፣ በፈተናም ጊዜ መጽናትን አትርፏል። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ ከአገልግሎት ውጪ በማህበራዊ ህይወት ውስጥ በሚፈጠሩ ጉዳዮች ወይም የህብረቱን መኖርና አገልግሎቱንም በማይፈልጉ ግለሰቦች ግፊት፡ እርስ በእርስ ቅሬታዎች ይፈጠራሉ፡ ይህም ቢሆን በዚሁ ስበሰባ ምክንያት በመነጋገር ስለሚፈታ ያስከተለው ጉዳት የለም።

የመዝሙር አጠናንና አቀራረብ፣የተመረጡ መዝሙሮች በደብተር ላይ በእጅ ይጻፋሉ፡ ዜማው በህብረት ተጠንቶ በቃል እስኪያዝ ድረስ በየግል ይደገማል፡ በጉባኤ ፊት ከመቅረቡም በፊት አንድ ጊዜ አሰላለፍና አቀራረቡ ይፈተሻል፡ ማስተካከያ ተደርጎ በጉባኤው ፊት ተሰልፈው በመቆም በየሳምንቱ ለእለቱ የሚስማማ፣ የጉባኤውን መንፈስ፣ የሚያረካ፣ ህሊናን የሚሰበስብ፣ ቀጥሎ ለሚዘራው የእግዚአብሔር ቃል ልቦናን የሚያለሰልስ መዝሙር ለማቅረብ ይሞከራል። ከመዝሙር በተጨማሪ በበዓላት ጊዜ ወረብ ይቀርባል፡ ወረብን ለመዘምራኑ በማስጠናት፣ ዜማውንና እንቅስቃሴውን በማለማመድ፣ መዝሙሮችንም በማጻፍና በማስጠናት፣ ዮናስ ብዙነህና ጽዮን አክሊሉ ጠንካራ መሠረት ጥለዋል። ከነሱ ቀጥሎ እህታችን ወ/ሮ መሠረት ኃይሉ የመዝሙርና የወረብ ዜማዎችን በማስጠናትና በመምራት እስካሁን ድረስ ታገለግላለች። በመዘምራኑ ደንብ መሠረት በቃል ሳያጠኑ በጉባኤ ፊት መቆም ክልክል ነው። ይህ ጠንካራ ዝግጅት ለሰ/ት/ቤታችን ብቻ ሳይሆን በሌሎች አድባራት በሚደረጉ ክብረ በዓላት ላይ ለበዓሉ ድምቀትን ያጎናጽፈዋል። በዚህም የኑርንበርግ ቅ/ስላሴ መዘምራን በየአድባራቱ አለቆችና መዕመናን ዘንድ እንደጥሩ አራአያ ይጠቀሳሉ።

የኑርንበርግ መዕመናን

የኑርንበርግ ቅ/ሥላሴ ሰ/ት/ቤት መዕመናንን የምገልጽበት ቋንቋ ባላገኝም ከብዙዎች ጥሩ አንደበትን፣ ታላቅ ማዕረግን፣ ወይም ስልጣንን አይተው ከሚመላለሱና ድርሻቸውንም ከማይወጡ መዕመናን በጣም ይለያሉ – ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት አንዱንም በጥቂቱ እንኳን የሚወክል አገልጋይ በመካከል ሳይኖር „ሁለትም ሦስትም ሆናችሁ በስሜ ካላችሁ እኔ በመካከላችሁ እገኛለሁ“ ማቴ፣18.20 ያለውን በሙሉ ልብ በማመን በየሳምንቱ ስዓታቸውን አክብረው የሚሰባሰቡ፣

– ታላቅ መንፈሳዊ ስነሥርዓት ያላቸው፣ ታናናሽ የሆኑ አገልጋዮቻቸውን የሚያከብሩ፣ በተጎላደፈ አንደበት ለሚነገራቸው ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ነው ብለው በማመን የልቦናቸውን ጆሮ ሰጥተው በጸጥታ የሚያዳምጡ፣

– በአጋጣሚ እንኳን አስቸኳይ የሆነ የገንዘብ እርዳታ ሲያስፈልግ በለጋስነት አስደናቂ ሥራ የሚሰሩ

– ከሰ/ት/ቤታችን ጀምሮ በቤ/ክን አባቶች መካከል በሃገር ላይም ችግሮች ሲከሰቱ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ ነገሮችን በጥሞና ከማየትና የሚገባቸውን በአግባቡ ከመወጣት በስተቀር የአጵሎስ የጳውሎስ በማለት ከአበደው ጋር የማያብዱ፣

– ለበዓላትና ለተለያዩ ዝግጅቶች የመስተንግዶ፣ የጉልበትና የገንዘብ እርዳታ በተጠየቁ ጊዜ በረከቱ እንዲደርሳቸው ከመሽቀዳደም ውጪ ልመና የማያስፈልጋቸው፣ እንግዳ በመቀበልና በመሸኘት እቃ በመገዛትና በመመለስ መኪናዎቻቸውን ሁሉ ለአገልግሎት የተሰጡ፣

– በቤ/ክን ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ተሳትፏቸውም የወንጌልን አላማ የያዙ በየቦታው በአራዕያነት የሚጠቀሱ የእግአብሔር ሰዎች ናቸው።

የበዓላት ጉዞና አከባበር

በጀርመን ውስጥ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት በአብዛኛው ለክብረ በዓል ጉዞ ይደረጋል፡ በተለይም ራቅ ወዳለው(ወደከለኝ ደ/ሰላም ቅሚካኤል) ጉዞው በትልቅ የህዝብ ማመላለሻ(በአውቶቡስ) ነው። ይህ የቡስ ጉዞ ረጅም ስዓት የሚፈጅ፣ ነገርግን የማይሰለች፡ በውስጡ የተለያዩ መርሃግብሮች የሚካሄዱበት ጠባብ የጉባኤ አዳራሽ ነው ማለት ይቻላል። የዚህ አዳራሽ መድረክ ለሁሉም ታዳሚዎች ክፍት ነው፡ በዚህ መድረክ ላይ ሁሉም በየተራ ማገልገል ይችላል፡ ጥያቄ ያለው ይጠይቃል፣ መልስ ያለው ይመልሳል፣ መዝሙር ያለው ይዘምራል፣ ጽሑፍ ያለው ያነብባል፣ ግጥም ያለው ይገጥማል፣ ትምህርት ያለው ያስተምራል፣ አይን አፋሩ አይኑን የሚገልጥበት ፈሪው የሚደፍርበት መድረክ ነው። አንዳንድ ጊዜም ራሳቸውን በትሕትና ካባ ውስጥ የደበቁ ለወንጌል አገልግሎት ብቁ የሆኑ ወንድሞች የሚጠመዱበት መረብም ነው። ለምሳሌ ዛሬ በወንጌል አገልግሎት የሚራዳው ሃብታሙ ታምራት የተገኘው ከዚህ ጉባኤ ውስጥ ነው። በግማሽ መንገድ ላይ ስንደረስ ከጠባቧ አዳራሽ ወጥተን በየጥላው ስር በቡድን በቡድን ቆም ብለን፣ ትኩስና ነፋሻ አየር እየተመገብን፣ እህቶቻችን ያዘጋጁልንን ጸበልና ጸዲቅ እየቀማመስን፡ ለግማሽ ስዓት ያህል ተናፈሰን ተንቀሳቃሽ ወደሆነችው አዳራሽ እንገባለን፡ የጀመርነውን ሳንጨርሰው ድካም ሳይሰማን በቅዱስ ሚካኤል በር ላይ ቀጥ ትላለች። ብዙዎቹ ይህንን ጉዞ ከሚጓዙበት በዓል ያላነሰ ይናፍቁታል። በሩ ሲከፈት ከማሰሪያው እንዳፈተለከ ነጭ ጥጥ ሁሉም በአንድነት ዝርግፍ ይልና ወደ ቤ/ክኑ በር በምታስወርደው አነስተኛ ደረጃ ቁልቁለቱን ሲወርድ ከሩቅ ለሚያይ የሃብታም መንጋ ይመስላል። ቁልቁለቷ እንዳለቀች በበሩ ፊት ለፊት ሁሉም በአንድነት በቅ/ሚካኤል እግር ስር እንደኢያሱ ሲደፋ፡ኢያ፣5.20 እውነትም እረኛቸው አጥግቦ ያስመሰጋቸውን የሃብታም በጎች መንጋ ይመስላል። „እኔ የበጎች በር ነኝ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል“ ዮሐ፣10.9 እንደተባለ የኑርንበርግ ቅ/ስላሴ በጎች በበሩ ዘልቀው ሲገቡና ከሌሎቹ ጋር ሲቀላቀሉ የቅ/ሚካኤል አዳራሽ ልፈንዳ፣ ልፈንዳ፣ ትላለች፡ ግን አትፈነዳም፡ እንዲያውም ስጋዊዉንም መንፈሳዊዉንም ምግብ እየመገበች፡ አንዱን በአንዱ ላይ አደራርባ በሙቀት ታሳድራቸዋለች። በነጋታው ታቦቱ ሲነግስ የኑርንበርግ መዕመናን ጆሯቸው ብዙ መዝሙር የጠገበ ስለሆነ፡ በተለይ ከመዘምራኖቻቸው ጋር ሲቀላቀሉ፡ ሁሉም ዘማሪያን ይሆናሉ፡ በዚህ ላይ ብዛታቸው ሲጨመርበት፡ ለበዓሉ ልዩ ውበትና ድምቀት ይሰጡታል።

የኑርንበርግ ቅ/ስላሴ ፅዋ ማህበር

በ፲፱፻፹፱ (1997) ዓ.ም ማህበሩ ተመስርቶ ለሐምሌ ስላሴ በማህበርተኛው ስም ጸበል ጸዲቅ ተዘጋጅቶ ተመረቀ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ልዩ ልዩ ቱሩፋቶችን በማከናወን ላይ ይገኛል። በተላያዩ አጋጣሚዎች በሃገራችን በሚከሰቱ ችግሮች በአጠቃላይ የሰ/ት/ቤታችን መዕመናን ከሚያደርጉት አስተወፅኦ በተጨማሪ፡ በፅዋ ማህበሩ ስም የተቻለውን ያደርጋል። ለምሣሌ፣- ድርቅ በተከሰተ ጊዜ፣ ለተለያየ መንፈሳዊ አላማ ከሃገርቤት ለሚመጡ አባቶችና ወንድሞች ለግላቸውና ለሚያገለግሉበት ተቋም ማጠናከሪያ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ይሰጣል። ከዚህ በተለየ መልኩ ጥንታዊያን ገዳማትን፣ አድባራትንና የአብነት ት/ቤቶችን ለማደስና ለማጠናከር፣ መነኮሳቱ፣ የአብነት መምህራኑና ተማሪዎቹ የአመት ልብስ የእለት ጉርስ በማጣት ምክንያት እንዳይበተኑ፣ ዘላቂ የሆነ የገቢ ምንጭ ለማስገኘትና እራሳቸውን ለማስቻል፣ በማህበረ ቅዱሳን ከተጠኑና ለጋሽ ከሚጠባበቁ በርካታ ጥናቶች(ፕሮጀክቶች) ውስጥ አንዱን ሙሉ ለሙሉ የፅዋ ማህበራችን የሚያስፈልገውን የገንዘብ ወጪ በመሸፈኑ ተግባራዊነቱን አግኝቷል። እንዲያውም ለዚህ የተመደበው ገንዘብ በመትረፉ ለሌላ ተጀምሮ ላላለቀ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ውሏል። የኑርንበርግ ቅ/ስላሴ ፅዋ ማህበር በየወሩ ጸበል ጸዲቅ እያዘጋጀ የሚመገባቸው ነዳያን በአካባቢው ባይኖሩም፡ በእለቱ የተገኙት መዕመናን በሙሉ ከበረከቱ እንዲሳተፉ በማድረግ መንፈሳዊ ወንድማማችነትንና ማህበራዊ አንድነትን በማጠናከር፡ የፅዋ ማህበር ደንብና ትውፊትንም ጠብቆ ለማቆየት ጥረት እያደረገ እስካሁን ደርሷል።

የአገልጋዮች እድገትና መጠናከር

ከሐምሌ ፲፬ ቀን ፲፱፻፹፰ (21.07.1996) እስከ ፳ ቀን ፲፱፻፹፰ (26.07.1996)ዓ.ም ቀሲስ መስፍን በሙኒክ ያዘጋጁት የተምሮ ማስተማር ሴሚናር ነበር። በዚህ ሴሚናር የሚሳተፉ ከጠቅላላው የጀርመን ግዛቶች ሰ/ት/ቤቶችና አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ወጣቶች ተጋብዘው ወንዶችና ሴቶች ሁለትም ሦስትም እየሆኑ ታድመዋል። በዚሁ መሠረት ከኑርንበርግም ሦስት ወጣቶች ሆነን በጠቅላላው ሃያ ሦስት(23) ተሳታፊዎች ነበርን። ይህ ሴሚናር ለአንድ ሳምንት የዘለቀና በጥሩ ዝግጀት ተካሂዶ የተጠናቀቀ ከመሆኑም በላይ፡ ለአንዳንዶቻችን በሥጋወ ደሙ ለመኖርና ለአገልግሎት የሚረዱ ጠቃሚ ቁምነገሮችን ለመገብየት የመጀመሪያው የምህረት በር ሆኖልናል። በዚያን ጊዜ ዘነበን ፕሮግራም በመምራት
አልፎ አልፎም በማስተማር ያግዙት የነበሩት ዮናስ፣ ዳንኤልና ዳዊት በተለያየ ምክንያት እንደአጀማመራቸው አልገፉም። ስለዚህ ዘነበ ብቻውን መርቶ ያስተምር ነበር። ይህ ሁኔታ በመዝሙር ክፍል ውስጥ ያለነውን አባላት፡ ልጁ፣ እክል ቢገጥመው ማን በጉባኤው ፊት ይቆማል? በማለት ያስጨንቀን ነበር። ስለዚህ አንዳንዶቻችን እራሳችንን ለአገልግሎት ማዘጋጀት ትልቁ ትኩረት ሆነ።

ዘነበ
በ፲፱፻፺ (1997) ዓ.ም በቀሲስ መስፍን አሳሳቢነት በሙኒክ ቅ/ገብርኤል የአውሮፓ ሊቀጳጳስ ከነበሩት ከብጱዕ አቡነ ዮሐንስ እጅ የዲቁና ሹመት ተቀበለ። ዲ/ን ዘነበ በዚሁ አገልግሎቱን ቀጥሎ ታህሣስ ፲፱፻፺፫ (2000) ዓ.ም ሃገር ቀየረ። ይህንን ያደረገው በድንገት ነበረ፡ የእርሱን ቦታ ለመሸፈን ደግሞ ብቃት ያለው ከመካከላችን አልነበረም። ሁላችንም ተደናግጠናል። ብዙዎቹ ዲ/ን ዘነበ ከሌለ ጉባኤው ይፈታል የሚል ግምት ነበራቸው። ግን በእግዚአብሔር ቸርነት እርስ በእርሳችን እየተደጋገፍን አገልግሎቱ ቀጠለ፡ ጉባኤውም አልተፈታ፣ ቁጥሩም አልቀነሰ። የኑርንበርግ መዕመናን ወንጌል የገባቸው ወደቤ/ክን የሚሄዱት ሰውን ፍለጋ ሳይሆን አላማቸውንና የሚፈልጉትን የሚያውቁ መሆናቸውን የተረዳሁት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው። በመዕመናን ምርጫ በዲ/ን ዘነበ ቦታ እኔ በኮሚቴው ውስጥ አባል እንድሆን ተደረገ።

የዘነበን ድንገት መሄድ ትምህርት ስለሆነን፡ በሰ/ት/ቤታችን የአገልጋይ እጥረት እንዳይኖር እርስ በእርስ መነቃቃቱ የበለጠ ተጠናከረ። አልፎ አልፎም ከማህበረ ቅዱሳን የሚመጡ ወንድሞች ኮርስ እንዲሰጡን በማድረግ ለአገልግሎት የሚበቁ በርከት ያሉ ፍሬዎች ተገኝተዋል። ለምሳሌ በዚያን ወቅት የመዝሙር ክፍል አባላችን የነበረው ብርሃኑ አበበ የአሁኑ አባ ገ/እግዚአብሔር ከዚህ ተነስተው በአሁኑ ስዓት በሃገራቸው ገዳማት ውስጥ በምናኔ ይገኛሉ። ወንድሞቻችን ኒቆዲሞስ ገ/አማኑኤል፣ መለሰ ደሌሳ፣ ሃብታሙ ታምራት፣ አቶ ጌዲዎን የማነ አቶ ፋሲል ኃ/ማርያም እና አቶ አበበ እሸቴ ደግሞ እንደየደረጃቸውና እንደየ አቅማቸው መርሃግብር በመምራትና በማስተማር በአሁኑ ስዓት ይሳተፋሉ።

ጥቅምት ፲ ቀን ፲፱፻፺፭ (20.10.2002) ዓ.ም በሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ አሳሳቢነትና ትእዛዝ በደብረሰላም ቅ/ሚካኤል ቤ/ክን ከብጹእ አቡነ ሙሴ የዲቁና ማዕረግ ተቀበልኩ።

ቄስ ገ/ስላሴ (አቦይ ቀሺ)

በ፲፱፻፺፪ (1999) ዓ.ም በሚኖሩበት የመጠላያ ጣቢያ አንስባህ የሚኖሩ
የቤ/ክን ልጆች ስላሉ በእነርሱ አማካኝነት የኑርንበርግ ቅ/ስላሴን ሰ/ት/ቤት ተዋወቁ። ጉባኤያችን በየሣምንቱ በመስቀል መባረክ ጀመረ። ተአምረ ማርያም በማንበብ ኪዳንና ወንጌሉን በመጸለይ በጸሎት ከፍተው በጸሎት የሚዘጉ አባት ተገኙ። እሳቸውም በጣም እረኩ፣ መዕመናንም ተደሰቱ፣ ከዚህም በላይ መምህረ ትህትና መበሆናቸው ከሁሉም አክብሮትና ፍቅር ተቸራቸው። በወቅቱ ለስብከተ ወንጌል ከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ ስለሚደረግ የብዙ ሰው ልቡና ለንስሀ የቀረበ ነበር። ግን የአባታችን የቀሲስ መስፍን መኖሪያ ሙኒክ ስለሆነ በተፈለጉ ስዓት ለማግኝት አይቻልም ነበር። ሲመጡም አገልግሎታቸውን ፈጽመው በችኮላ መመለስ ግድ ስለሚሆንባቸው ተረጋግተው ሰውን ማነጋገር አይችሉም ነበር። አቦይ ግን በተፈለጉ ስዓት ይገኛሉ፣ በየቤቱ ሔደው ጸበል ይረጫሉ፣ ንስሐ ይቀበላሉ፣ እንቅልፍ ድካም የማያታልላቸው ትጉሕ የጸሎት ሰው በመሆናቸው፡ በጸሎት እንዲራዱት ያሳሰባቸውን በሙሉ በስም ይዘው ሲጸልዩ ያድራሉ። በዚህ የተነሳ በሂደት አገልግሎት ላይ ያሉትን በሙሉ፡ እና በርካታ መዕመናንን ለሥጋ ወደሙ አብቅተዋል። አቦይ ከጥቂት ዓመታት ጀምረው ደግሞ ለኤርትራውያን ወንድሞቻችን በዚሁ በኑርንበርግና በሌላ ቦታም አገልግሎት ይሰጣሉ። እንዲህም ኾነው በተለይም እሁድ እሁድ ባለቻቸው ደቂቃ እንደምንም ብለው ሮጠው ሥላሴን ሳይሳለሙ ልጆቻቸውን ሳይጎበኙ መዋል ደስ አይላቸውም።(ፎቶ)

ህፃናት

ሰ/ት/ቤታችን ተጠናክሮ በየሳምንቱ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ጥቂት ቆይቶ ሳያሰልሱ የሚሳተፉ ሁለት ህፃናት ነበሩ (ቴዲና ሊያ)። በእናቶቻቸው ጉያ ተሸጉጠው ሳይሰለቹ ጉባኤው ተጀምሮ እከሚያልቅ ድረስ በጥሞና ይከታተላሉ። አፋቸውን መፍታት እንደጀመሩ እንደሁሉም ሰው እጅ አውጥተው የሚወዱትን መዝሙር ያስመርጣሉ ቴዲ ኮልተፍ ባለ የህፃን አንደበቱ „ዝ.ዝ.ዝ.ዝም አትበሉ“ ይላል። ሊያ ደግሞ „አማን በአማን“ ስትል፡ በአድናቆት ጭምር መዝሙሩ በድምቀት ይዘመራል። በጊዜው የነበርን ሰዎች ዛሬ ላይ ሆነን ያንን ዘመን ስናየው በአሁን ስዓት በሌላ ቦታ በሌላ አለም ውስጥ ያለን ይመስላል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እዚች ቤት ውስጥ እጅግ በርካታ ህፃናት ተጠምቀዋል። በቁጥር ለማስቀመጥ ለጊዜው ይህ ጸሑፍ ሲዘጋጅ የተሰባሰበ መረጃ የለም፡ በግምትም ማስቀመጥ አዳጋች ነው፡ ምናልባትም በቅርቡ ከመዕመናኑ የህፃናቱ ቁጥር ሳይበልጥ እንደማይቀር ይገመታል፡ ምክንያቱም ከሁለት እስከሦስት ያልወለዱ ቢኖሩ በጣም ጥቂቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

እነዚህ ህፃናት ከመብዛታቸው የተነሳ፡ ጉባኤውም እንዳይረበሽ አነሱም ሃይማኖታቸውን እየተማሩ በስርዓት ማደግ እንዳለባቸው ግልጽ ቢሆንም፡ ይህንን ማድረግ ደግሞ በጣም ከባድና አስቸጋሪ ነው። ሃላፊነት መውሰድ፣ መስዋዕትነት መክፈልን ይጠይቃል። ብዙጊዜ እንደዚህ አይነት ክፍተቶች ሲፈጠሩ ቀዳዳውን ለመሸፈን መዘምራን ግንባር ቀደም ናቸው። በመሆኑም ከመከከላቸው አንዷ እህት ወ/ሪት የአሁኗ ወ/ሮ ቀዳማዊት ተሰማ ለራሷ መማርን ማስቀደስን ለህፃናቱ ስትል መስዋዕት በማድረግ፡ ለብቻቸው በአንድነት ሰብስባ ታጫውታቸዋለች፣ እንደየእድሜና አቅማቸው ፊደል ታስቆጥራቸዋለች፣ መዝሙር ታስጠናቸዋለች። በበዓላት ጊዜ ስርዓት ይዘው ተሰልፈው በጉባኤ ፊት ቆመው በሕፃን አንደበት እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑት የሚያይ ሁሉ የደስታ እንባ ይተናነቀዋል።(ፎቶ)

የሰ/ት/ቤቱ ፈተና

በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስርዓት መሠረት ማንኛውም መንፈሳዊ ተቋም ሲመሠረት በቦታው የሚደረገውን እንቅስቃሴ በበላይ ሆኖ የሚቆጣጠር የተጣመመውን የሚያቃና ጥሩውን የሚያጎለብት አንድ አባት የግድ ያስፈልጋል። የዚህ ቦታ
ትልቁ ፈተና በመካከላችን አባት ያለመኖሩ ጉዳይ ነበር። የበላይ አስተዳዳሪያችን ቀሲስ መስፍን ገ/ማርያም ቢሆኑም፡ የሚኖሩት በርቀት ስለሆነ ለአገልግሎት በሚመጡ ጊዜ ከሚያዩት ውጭ በየሣምንቱ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በአይናቸው አያዩም። በዚህ የተነሣ አሳቸውንም ሆነ እኛን ግራ የሚያጋቡ ነገሮች መፈጠራቸው አልቀረም። እዚህ ላይ ትዝ የሚለኝን አንድ ነገር ልጥቀስ፣ አንድ ቀን በጉባኤው ፊት ቆመው እዚህ ስለሚሰጠው አገልግሎት ሲናገሩ „የማየው ነገር ጥሩ ነው የምሰማው ደግሞ ሌላ ነው“ አሉ። ይህ ሁኔታ አለመግባባትና ችግሮችን እያስከተለ በመምጣቱ፡ እራስን ለመቻል ለሚደረገው እንቅስቃሴ ምክንያት ሆኗል። አሁን ያሉት ካህን መሪጌታ ዳዊት ሃላፊነቱን እስከሚረከቡበት ጊዜ ድረስ በርካታና አስቸጋሪ ፈተናዎች አልፈዋል።

ራስን የማስቻል እንቅስቃሴ

በፈረንጆቹ 2000ዓ.ም በፍራንክፈርት እንድ የካህናትና የሰበካ ጉባኤ አባላት ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ እኔም ነበርኩ። በጀርመን የኢትዮጵያ ኦ.ተ.ቤ.ክን ሊቀካህናት ደክተር መረዓዊ ተበጀ በዚህ ስብሰባ ላይ ካቀረቧቸው አጀንዳዎች አንዱ የሀምቡርግና እሽቱትጋርት ሰ/ት/ቤቶች ወደ ቤ/ክንነት ተለውጠው እራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ የሚል ነበር። በዚህ ጊዜ በተቆታ ስሜት እጀን አወጣሁ፡ ሲፈቀድልኝ „ምነው ስለኑርንበርግ ሲወራ አልሰማ? በመዕመን ብዛት እንደሆነ ኑርንበርግ ከሁላችሁም አያንስም። ለመሆኑ ራስን ለመቻል መስፈርቱ ምንድነው?“ በሚል አጭር ጥያቄ አቀረብኩ። ሊቀካህናቱ ምንም ሳያመነቱ „ምንችግር አለ፣ እናንተ ከበረታችሁ፣ ዋናው የእናንተ መበርታት ነው እናቴ! እናንተ ከበረታችሁና ገንዘብ ካሰባሰባችሁ፡ ከነዚህ (ከሀምቡርግና ከእሽቱትጋርት) ቀጥሎ የእናንተ ይሆናል“ አሉ፡ በአባታዊና በሚያረጋጋ ድምፅ።

ቀሲስ መስፍን በስብሰባው ላይ ስለነበሩ ኑርንበርግ ሲመጡ በኮሚቴው ፊት ሃሳባቸውን እንዲሰጡ በማሰብ ሊቀ ካህናቱ የተናገሩትን አስታወሰኳቸው። እሳቸውም የሊቀካህናቱን ሃሳብ በመድገም „እናንተ ከተባበራችሁና አንድ ሃሳብ ከሆነችሁ የማይሆን ነገር የለም…“ በማለት ሰፋ ያለ የሚቀሰቅስና የሚያበረታታ አስተያየት ሰጡ። ቀጣዩ ሥራ የእንቅስቃሴውን አጀማመር ማመቻቸት ነበር።

ቀደም ብሎ ጥሩ በማገልገል ላይ የነበረችው ወ/ሮ ወርቄ ሃገር በመቀየር ስትሰናበት በእሷ ቦታ ተተክቶ፣ በወቅቱ የነበሩት የኮሚቴ አባላት፣- አቶ ካሳሁን እሸቴ ሰብሳቢ አቶ ካሱ ለገሠ ጸሐፊ አቶ ተፈሪ ገንዘብ ያዥ ወ/ሪት አቦወርቅ ብርሃኔ አባል መታፈሪያ ወ/ፃድቅ አባል ነበርን።

የካቲት ፰ ፲፱፻፺፬ (16.02.2001) ዓ.ም ከወ/ሪት አቦወርቅ በቀር አራታችን በተገኘንበት ይህ አጀንዳ ቀረበ። ስምምነት ላይ ተደረሰና በሚቀጥለው ሳምንት ለሕዝቡ እንዲነገርና ቅስቀሳ እንዲጀመር ወስነን ተለያን። በሳምንቱ ለጉባኤው ተነገረ። ሰብሳቢውም ጸሐፊውም ራስን ለመቻል የሁሉም ትብብር አስፈላጊ መሆኑን የየበኩላቸውን ተናገሩ። እኔም ሊቀካህናቱ እንደተናገሩት ወሳኙ የገንዘብ አቅም ስለሆነ ሁላችንም እጃችንን ከዘረጋን በአጭር ጊዜ እንደሚሳካና የራሳችን በመካከላችን የሚኖር አባት በአጭር ጊዜ ሊኖረን እንደሚችል ለዚህም ቃል እንደተገባልን አሳወቅሁ። ከዚያ በየሳምንቱ በተለያየ አቀራረብ ጉባኤውን ማሳሰብና መቀስቀሱ ቀጠለ። የገንዘብ ያዡ አቶ ተፈሪ በሥራ ጸባይ ምክንያት መቀጠል ስላልቻለ ሃላፊነቱን አስረከበ።

ታህሳስ ፲፱፻፺፬ (2001) ዓ.ም ቀሲስ መስፍን በተገኙበት አቶ አበበ እሸቴ በመዕመናን ተመርጦ በቦታው ተተካ። ከዚህ ጀምሮ የቅስቀሳው ስራ በአዲስ መልክ ተጠናከረ። አበበ መዝገቡን እየመረመረ በጉባኤም በግልም ማነቃቃቱን ተያያዘው። በዚሁ ሁኔታ እንደቀጠልን መዕመናን እርግጠኛ እንዲሆኑና እጃቸውም እንዲፈታ፡ ገንዘቡ ወደሙኒክ መተላለፉ ቀርቶ እዚሁ በመዕመናን ተወካይ የሚንቀሳቀስ የባንክ ሂሳብ እንዲከፈት ለበላይ አካል ጥያቄ ቀረበ። በሊቀካህናቱ በጎ ፈቃድ፣ በሰ/ት/ቤታችን ስም፣ በኮሚቴው ሰብሳቢና በገንዘብ ያዥው ውክልና ግንቦት  ፲፭ ቀን ፲፱፻፺፬ (23.05.2002) ዓ.ም የባንክ ሂሳብ በኑርንበርግ ተከፈተ። ሊቀካህናቱም ተጨማሪ ተስፋ ሰጡ „በአንድ አመት ውስጥ ይህንን(…) ያህል ገንዘብ ከሰበሰባቸሁ አንድ መነኩሴና ታቦተህጉ እንዲመጣላችሁ ሂደቱ ይጀመራል“ የሚል ሲሆን፡ እኛም ያለውን ተስፋ ለህዝባችን እየነገርን ስንንቀሳቅስ አመቱ ደረሰ፡ የተሰበሰበውም ገንዘብ የተጠየቀውን እጥፍ ለመሆን ተቃረበ። ይህ መረጃ እንደደረሳቸው ሊቀካህናቱ ታቦተ ህጉን የማስመጣት ሂደት ጀመሩልን። አገልጋይ የሚሆኑት ካህን ግን ባያስተዋውቁንም ከቅርብ አካባቢ እንደሚያገኙልን ተስፋ ሰጡን።

የስሉስ ቅዱስ ታቦተ ህግ በኑርንበርግ

የሐምሌ ሥላሴ ፲፱፻፺፭ (12.07.2003) ዓ.ም በብጹዕ አቡነ ዮሴፍ አማካኝነት ስሉስ ቅዱስ ኑርንበርግ ገቡ። ደስታ ሆነ፡ ብዙ ጊዜ አመታውዊ በዓል ስናከብር ከሩቅ መጥተው የሚሳተፉ አንዳንድ መዕመናን ዝግጅቱ ስለሚያረካቸው „ኑርንበርግ ካህን ባይኖርም ስሉስ ቅዱስ በአካል አሉ“ ይላሉ። እውነትም አብርሃም ቤት በአካል እንደገቡ ሁሉ እኛም እምስኪኖቹ ጓዳ በአካል የገቡ ያክል ነው አብዛኛዎቻችን የተሰማን። ያቺ የመጀመሪያ ቀን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ይችን ቦታ የጎበኘባት ምንኛ የተባረከች ቀን ነበረች፣ እኛ የመጀመሪያ አባት ከዚያች ቀን ጀመረው ወጥተው ወርደው ያገለገሉት፣ ያቺ የመጀመሪያ ወጣት ለዚያች የመጀመሪያ ቀን ምክንያት የሆነች፣ በህይወት ቆይተው ይችን የዛሬዋን ቀን በድጋሜ ሲያዩ ምን ይሰማቸው ይሆን?

ይህ በዓል ቀሲስ መስፍን ከዚህ ቦታ ሃላፊነት የሚሰናበቱበትም ጭምር ስለሆነ፡ በመዕመናኑ ስም ኮሚቴው ስጦታ አዘጋጅቷል። እንዲሁም ይህንን ቦታ ያለመሰልቸት አስከዛሬ ድረስ እንድንገለገልበት ለፈቀዱልን ለሳንት ኩኒጉንድ ቤ/ክን ሃላፊ ለሆኑት ቄስም ስጦታ ተዘጋጅቷል። የበዓሉ ዕለት ማታ ከነበሩት ልዩልዩ መርሃግብሮች አንዱ ይኸው የስጦታ መርሃግብር ነበር። የተዘጋጀው ስጦታ ሲቀርብ አቀራረቡ ትርጉም እንዲኖረው ታስቦበታል። ስለዚህ ከሰማይ ለወረደው ለመና መገኛ እንደሆነቸው መሶብ፡ በአነስተኛ መሶብ ውስጥ በክብር ተቀምጧል። ስነስርዓቱ ተጀመረ፡ ከላይ እንደተባለው የመጀመሪያዋን ቀንና የመጀመሪያዎቹን ሰዎች፡ ያለፉበትንም መንገድ ለዚህ ያደረሳቸውን የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ፡ በመጠኑ ለመዕመናን ተገልጾ፡ የዛን ጊዜዋ ወ/ሪት የአሁኗ የልጆች እናት ወ/ሮ አብነት እንደመጀመሪያው ሁሉ በመጨረሻም አስተናግዳ ልትሸኛቸው መሶቧን በክብር ይዛ ቀረብ አለች። በሊቀ ጳጳሱ እጅ ተበረከተላቸው። መሶቡ ተከፈተ፡ ለካስ ያ በመጀመሪያ ቀን አብነት የተሳለመችው የእጅ መስቀል ነበር፡ የአንገት መስቀልም አለበት፡ ቀሲስ መስፍን በሰከንዶች ውስጥ በርረው ኑርንበርግን የረገጡባት የመጀመሪያዋ ቀን ላይ ያረፉ ይመስላሉ። የሆነ ነገር ለመናገር ፈልገው ድምፅ ማጉያው ወዳለበት ቀረቡና፡ ተናገሩ፣ ተናገሩ፣ ተናገሩ፣ ብዙ ተናገሩ ቃላቶች ግን አላወጡም። ከቃላቶች ይልቅ እንባቸው ነው ብዙ የተናገረው። ተመልሰው በወንበራቸው ላይ ተቀመጡ። ህዝቡም ተረዳቸው፡ የሁሉም ስሜት ተኮረኮረ፡ ሁሉም ከንፈሩን መጠጠ፡ ያለቀሱም አለቀሱ። ለነጩም ቄስ እንደዚሁ ከመጀመሪያ ጀመሮ ከእነሱ ጋር ያለውን ግንኙነት ያካሄደልን እሱ እንደሆነ በማስተዋወቅ አቶ ካሳሁን አበረከተ። የኑርንበርግ ቅ/ሥላሴ ቤ/ክን መዘምራን ተደሰቱ፣ ዘመሩ፣ ለታሪካቸው የሚስማማውን ቀደም ብለው ለረጅም ወራት የተዘጋጁበትን በያሬድ ዜማና ሽብሸባ የተዋበውን ወረብ አንቆረቆሩት።(ፎቶ)

ሀበነ እግዚኦ አእምሮ አእይንተ አእምሮ ወትረ ኪያከ ይርዓያ

ወአእዛንነሂ ቃለ ዘባህቲትከ ይስምዐ

ትርጉም፣-   አቤቱ አንተን ብቻ የሚያይ የአእምሮ ዐይን ስጠን

ጆሮዎቻችንም የአንተን ቃል ብቻ ይስሙ

አዎ እሱን ብቻ በማየት፣ የእሱን ቃል ብቻ በመስማት፣ በቸርነቱ ለዚህ በቅተዋልላ!

በነጋታው ቀሲስ መስፍን ሌላ ስጦታ ተበረከተላቸው። ለድካማቸው ሁሉ መታሰቢያ እንዲሆን „መለአከ ብርሃን“ ተባሉ። ከዚች ደቂቃ ጀምሮ ቀሲስ መባል ቀረ „መለአከ ብርሃን መስፍን ገብረ ማርያም“ በዓለ ንግሱ በደመቀ ሁኔታ፣ ተከናወነ ከዑደት በኋላ ታቦቱ ቆሞ፡ መለአከ ብርሃን መስፍን የመጨረሻውን የመሰናበቻ ንግግር አደረጉ።

አባ ላዕከማርያም መንግስቱ

በበዓሉ ዋዜማ ቅዳሜ ማታ ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ኮሚቴውንና በወቅቱ የነበሩትን ካህናት ሊቀ ጳጳሱን ጨምሮ ሰበሰቡን። ለቅ/ስላሴ አገልጋይ ይሆናሉ ያሏቸውን ቁመታቸው ዘለግ ያለ ወጣት መነኩሴ አስተዋወቁን። ሊቀ ጳጳሱም አገር ቤት እያሉ እንደሚያውቋቸው ተናገሩ። መነኩሴውም ፈቃደኝነታቸውን ሲጠየቁ „እታዘዛለሁ“ አሉ። አባ ላዕከ ለሁለት ጎራ በተከፈሉት አባቶቻችን ምክንያት አሜሪካ ባሉት አባቶች በሚመራው ፍራንክፈርት በሚገኘው መድኃኔ አለም ቤ/ክን ነበሩ። ከዚያ በእርቅ ወደዚህኛው እንደተመለሱ ነው ለኑርነበርግ የታጩት። እኛም ይህንን ዜና በተለያየ መንገድ ሰምተነው ስለነበር የእሳቸው እዚህ መመደብ በህዝቡ ስሜት ላይ ችግር እንዳይፈጥር ፈርተን ነበር። ሆኖም ግን አባቶቻችንን ቅር ከምናሰኝ እግዚአብሔር የፈቀደው ይሁን በማለት ኮሚቴው ምክክር አድርጎ ተቀበልን።

እሁድ ነሐሴ ፲፩ ቀን ፲፱፻፺፭ (17.08 2003) ዓ.ም አባ ላዕከን መልአከ ብርሃን ይዘዋቸው መጡ። በደመቀ ዝማሬ ታጅበው የደመቀ አቀባበል ተደረገላቸው። አባላዕከ ማርያም አገልግሎት እንደጀመሩ የእሳቸው ፍላጎትና የቤተክርስቲያኒቱ ፍላጎት አልተጣጣመም። ያለው እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ለእሳቸውም፣ ለመዕመናኑም፣ ለአገልጋዮቹም ሁሉ የማይመች ሆነ። ችግሩን ለመፍታትና ለማስተካከል ሊቀካህናቱ በሚመሩት የካህናት ስብሰባ ሳይቀር ብዙ ተሞከረ፡ ግን ውጤት አላስገኘም።

የመጀመሪያው የሰበካ ጉባኤ ምርጫ ግንቦት ፯ ቀን ፲፱፻፺፮ (2004) ዓ.ም እለተ ስሉስ ቅዱስ፣ ሊቀ ካህናት ደ/ር መርዓዊ ተበጀ የመጀመሪያውን የሰበካ ጉባኤ አባላት ለማስመረጥ በተያዘው ቀጠሮ መሠረት መጡ። ምርጫው ከመጀመሩ በፊት ቀደም ሲል በኮሚቴው መካከል በነበረው አለመግባበት የተነሳ ጭቅጭቅ የተፈጠረ ቢሆንም፡ ሊቀካህናቱ ነገሩን አረጋግተው ወደምርጫው ተገባ። በእኔ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ ጸሐፊውና ገንዘብ ያዡ ድጋሜ ተመርጠው ቢቀጥሉ ደስተኛ ነበርኩ። ምክንያቱም፣-

ጸሓፊው አቶ ካሱ ለገሠ በስራ ምክንያት ዘወትር ባይገኝም በተገኘባት ስዓት ለጊዜውም ለጉልበቱም የማይሳሳ፣ ማንኛችንም ብናዝዘው ምክንያት የማይፈጥርና በቅንነት የሚፈጽም ወንድም ነው። በስብሰባም ላይ ቃለጉባኤ ይይዛል አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ይህኛውንም ያኛውንም ሃሳብ አይነቅፍም አይደግፍም መጠነኛ የሆኑ የማስታረቂያ ሃሳቦችን ከማቅረብ ውጭ አብዛኛውን ጊዜ በማዕከላዊነት ዝም ይላል።

ገንዘብ ያዡ አቶ አበበ እሸቴ ደግሞ በስብሰባ ላይ ብዙ ጊዜ የሃሳብ ልዩነቶች ሲነሱ የሚያምንበትን ሓሣብ ይደግፋል በስብሰባ ደንብ መሠረት የሃሳብ ልዩነቶች በድምጽፅ ብልጫ የሚወሰኑ ቢሆንም፡ ብዙ ጊዜ ጭቅጭቅ ሚያስነሱት ነገሮች ግን ፍሬ ያላቸውና በድምፅ ብልጫ ለመለየት የሚመቹ ስለማይሆኑ፡ በመተማመን በመግባባት እንዲያልቁ እስከመጨረሻው ይገፋል። ሃላፊነቱን በሚመለከት ከተመረጠበት ጊዜ ጀምሮ በገንዘብ አያያዙና አሰባሰቡ እራስን ለመቻል በሚደረገው እንቅስቃሴ ያለምንም ተቀማጭ ገንዘብ ከዜሮ የጀመርን ስለሆነ በታላቅ ጥረት ከመዕመናን ትብብር ጋር የተጠየቀው የገንዘብ መጠን እንዲሟላ በማድረግ ራሳችንን ለመቻላችን ታላቅ ምክንያት የሆነ ወንድም ነው።

በሥላሴ ፈቃድ ሌሎች ጥቆማዎች ተካሂደው የሰ/ትቤቱና የመዝሙር ክፍሉ መስራች የሆኑት ወንድሞችና ለቤ/ክናቸው ፍቅርና ቀናኢነት ያላቸው ዘወትር ከጉባኤ የማይለዩ፣ በፅዋ ማህበር፣ በመስተንግዶና በተላያዩ አገልግሎቶች የሚሳተፉ እህቶች፣-

1. አቶ ዳንኤል ብርሃኔ

2. አቶ ዮናስ ብዙነህ

3. አቶ ይበልጣል አንድነት

4. ወ/ሮ አበባ እሸቴ

5. ወ/ሮ ፋንትሽ አበበ ተመርጠው ሊቀ ካህናቱ ምክር ሰጥተው በጸሎት ተዘጋ።

አዲሱ የሰበካ ጉባኤ፣-እንደአንድ ልብ አሳቢ እንደአንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን ተግባብቶ መሥራት ጀመረ። አባ ላዕከ የቀድሞው የኮሚቴ ሰብሳቢ ድጋሜ ካልተመረጠ አልሠራም፡ ብለው ስለነበር ይህ ፍርሃት ከውስጣቸው እንዲወጣና ከዚህኛውም ተመራጮች ጋር መሥራት እንደሚችሉ ለማግባባት ብዙ ሙከራ ተደረገ። ነገርግን አልተሳካም። አባ በ፲፱፻፺፯ (2005) ዓ.ም እኩለ ጾም ደብረዘይትን ቀድሰው ኑሮው እንዳልተመቻቸው በመግለጽ ሕዝቡን ተሰናብተው ሄዱ።

የኦዲተሮች ምርጫ፣- ኮሚቴው ተቀይሮ አዲስ የሰበካ ጉባኤ ሲተካ የእናት ቤ/ክንን የአሠራር ስልት ለመከተልና ከመእመናን ጋር ተማምኖ በግልጽነት ለመሥራት ሲባል አቶ ደረጀ ጉታ፣ ዮሐንስ(…) እና የኋላሸት ተሾመ ቋሚ ኦዲተሮች ሆነው ተመረጡ። ቀድሞ ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበረውን ሒሳብ አጣርተው ለህዝብ እንዲያቀርቡና ተተኪው አስተዳደር (ሰበካ ጉባኤ)እንዲረከብ ስለታመነበት፡ እነሱም እስከቻሉት ድረስ ሄደው የደረሱበትን፡ ማለትም ኑርንበርግ የባንክ ሒሳብ ከተከፈተ ጀምሮ ያለውን ወጪና ገቢ አጣርተው አቀረቡ።

የስላሴ ድንቅ ቸርነት

አባ ለዕከ ማርያም እንደሄዱ በጥቂት ሣምንት ውስጥ፡ ሊቀካህናት ዶ/ር መርዓዊ ስልክ ደውለው „አንድ ነገር ላማክርህ ነው፣ መሪጌታ ዳዊት እናንተ ጋር ተመድቦ ቢያገለግላችሁ ምን ይመስልሃል?“ አሉኝ፡ ጆሮየን ባለማመን „ምንአሉኝ?“ ያንኑ ደገሙልኝ „አባታችን ይኸ ነገር እውነት ነው? እኔ አላምንም ይህ የእግዚ አብሔር ድንቅ ሥራ ነው ሳይዘገይ ጎበኘን ማለት ነው….“ ቃላቶች እስኪአጥሩኝ ድረስ ደስ አለኝ፣ እሳቸውም ደስ አላቸው፣ „በል እንግዲህ ለጊዜው የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሲሆን መደረግ ያለበትን እናደርጋለን፣ በርቱ ተጠናከሩ“ አሉኝና ተሰነባበትን።

መሪጌታ ዳዊት ከፍያለው ከሌሎች ሦስት ጓደኞቻቸው ጋር ለከፍተኛ የቤ/ክን ትምህርት (ቲኦሎጂ) ተልከው በአይሽቴት ከተማ ይገኛሉ። ገና እንደመጡ ተዋውቀናል፡ ከዚያም አልፎ ተቀራርበናል፡ ቦታውም ለኑርንበርግ ቅርብ ስለሆነ ሁሉም እንደ ተመቻቸው እየመጡ ያገለግላሉ። ለጉባኤያችን ያላቸውን ፍቅርና አድናቆት፡ ብዙ ጊዜ ይገልጻሉ። እኛም እንወዳቸዋለን፡ ስለዚህ የሊቀካህናቱን ስልክ እንደዘጋሁ ወደመሪጌታ ደወልኩ። በእኛ በኩል መሪጌታ የእኛ አገልጋይ ይሆናሉ ብሎ አስቦ የሚያውቅ እንደሌለ ሁሉ እሳቸውም ድንገተኛ ጥያቄ ከሊቀካህናቱ ስለቀረበላቸው እሺም እምቢም ለማለት ቢከብዳቸውም፡ ፈቃደ እግአብሔርን መጋፋት ስለፈሩ ወደ እሽታው እንዳዘነበሉ ነገሩኝ። እኔም የበኩሌን ለመገፋፋት ሞከርኩ። አስቀድመው ቅስስና መቀበል ስለነበረባቸው ሒደቱ ተጠናቅቆ፡ ለዳግሚያ ትንሣኤ ሚያዚያ ፴ ቀን ፲፱፺፯ (08.05.2005) ዓ.ም ጣሊያን ሔደው ከብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ክህነት ተቀብሉ። በሳምንቱ ግንቦት ፯ ቀን ፲፱፺፯ (15.05.2005)ዓ.ም በእለተ ስሉስ ቅዱስ ከሊቀ ካህናቱ ጋር መጥተው ከመዕመናን ጋር ተዋወቁ። በእለቱ የጽዋ ማህበራችን ነበር፡ አዳራሹ ቄጠማ ተጎዝጉዟል፣ አጋጣሚ ሆኖ ተራው የወ/ሮ አብነት ነበር፡ በየአመቱ የእሷ ተራ ሲሆን ቄጠማ ይጎዘጎዛል። ዛሬ ቀሲስ ዳዊት ያችን መጀመሪያ ቀን በዚህ ቄጠማ ያስታውሷታል „ለእኔ መቀበያመስሎኝ ነበር“ እያሉ በቀልድ ያስቁናል።(ፎቶ)

መሪጌታ ዳዊት የቤ/ክንን ትምህርት ከልጅነታቸው ጀምረው አስከአሁን ድረስ ተምረዋል። በተለይም ደግሞ የዜማ ባለሙያ ናቸው። ታዲያ የኑርንበርግ መዘምራን በታቦቱና በመዕመናን ፊት ቆመው ሲዘምሩ መሪጌታ በመመሰጥ ያለቅሳሉ። ልጆቻቸውንም ይመርቋቸዋል፣ ያበረታቷቸዋል፣ አንዳንዶቻችን ደግሞ ይህንን ስንሰማ በትዝታ ፈረስ እንጋልባለን። ለመዘመር ስንወጣ የነበረ ፍርሃትና መሸማቀቅ፣ ዘምረን ስንቀመጥ የነበረ ትችት በተለይ የቅርብ ጊዜው ቦታ አይበቃም በሚል ሰበብ የነበረው የአገልግሎት እገዳ እየመጣብን፡ ከአሁኑ ጋር ስናነጻጽረው ግርም ይለናል። ዛሬም የምንገለገለው በዚያው ባልሞተ ቦታ ነው። ታዲያ ታቦቱም አልጠበበው፣ ካህኑም አልጠበባቸው፣ መዘምራኑም አልጠበባቸውም፣ ሁሉም የየድርሻውን በተመደበለት ስዓት ያገለግላል። አንዳንድ ጊዜ የመዕመናንና የመዘምራኑ ቁጥር አነስ ሲል፡ ካህኑ ይደነግጣሉ፣ „ምንሆኑ የት ሔዱ?“ ይላሉ። ለበጎቹ የሚጨነቅ ትጉህ እረኛ፣ዮሐ፣10.13-15 የሥላሴ ድንቅ ቸርነት ይሏል ይህ ነው።

መሪጌታ አሁን በያዝነው ፳፻ (2008)ዓ.ም ሁለተኛውን ዙር የሰበካ ጉባኤ አመራር አስመርጠዋል። እነሱም፣-

1. ፋሲካ ዳንኤል ምክትል ሰብሰሳቢ

2. ሙሉ መንግሰቱ ጸሐፊ

3. አቶ አህመድ ሲራጁ (ኃ/ሚካኤል) ገንዘብ ያዥ

4. ወ/ሮ ሰብለ እሸቴ ግንኙነት

5. ወ/ሮ አዲስአለም ከበደ ሒሳብ ሹም ሲሆኑ፡ እሳቸው በአስተዳዳሪነታቸው ዲ/ን መታፈሪያ የሰ/ት/ቤቱ ተወካይ በመሆን ሥራችንን ጀምረናል።

የራሳችን ህንፃ ቤክ/ን እንዲኖረን በብዙዎቻችን ጭንቅላት ሲጉላላ የነበረውን ሃሳብ እውን ለማድረግ፡ ይህንን ብቻ የሚያስፈጽም አንድ ኮሚቴ ከመዕመናን አስመርጠው አቋቁመዋል። እነዚህ የኮሚቴ አባላት፣-

1. አቶ አበበ እሸቴ

2. አቶ ቅባቱ ኮርታዊ

3. አቶ ዮናስ ብዙነህ

4. አቶ ዳንኤል ብርሃኔ

5. ወ.ሮ. ቀዳማዊት ተሰማ

6. ዲ/ን መታፈሪያ ወ/ፃድቅ በመሆን እንቅስቃሴ ጀምረናል

የኑርንበርግ
ቅ/ሥላሴ ቤ/ክን አመሠራረት እድገትና አካሄድ ከሞላ ጎደል ይህንን ይመስላል።

አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስፈጸመኝ እግዚአብሐዘር ይመስገን!

ዲ/ን መታፈሪያ ወ/ፃድቅ

Aethiopische Calendar

Announcement

Find us on Facebook

EOTC Hl. Dreifaltigkeit Kirchengemeinde Nuernberg, Aethiopisch, Tewahedo, Aethiopien, Ethiopia, Orthodox, Kidist Selassie
WP-Backgrounds Lite by InoPlugs Web Design and Juwelier Schönmann 1010 Wien